Thursday, January 31

ኢት/ዊ ሱራፊ ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት እይታ


አንድ ለቅምሻ የ‹ኢትዮጵያዊው ሱራፊ› መግቢያ መግቢያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነ ቦታ ካላቸው ጥቂት ቅዱሳን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ የታላላቅ አባቶች የቆብ አባት፣ የታላቁ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መሥራች፣ በሐዋርያዊ አገልግሎት አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ያዳረሱ፣ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ ደቀ መዝሙሮቻቸው ገድላቸውን የጻፉላቸው አባት ናቸው፡፡ ‹‹እጨጌዎች›› በኢትዮጵያ ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የነበራቸውን ቦታ ስንመለከት፣ ዛሬም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች ‹‹እጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው መጠራታቸውን ስናይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ለመገመት ያስችለናል፡፡ ካፕላን እንደሚለውም ‹‹ከኢትዮጵያ ውጭ በግብጽ፣ በሮም በኦፊሴል የሚከበሩ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ናቸው››፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የልደት በዓላቸውን የምታከ ብርላቸው አራት ቅዱሳን ብቻ ናቸው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንና የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰጠቻቸው ክብር ጻድቁ ከኢትዮጵያ ውጭ ያላቸውን ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ መንፈሳውያን ማኅበራት መካከል አንዱ ‹‹ማኅበረ ተክለ ሃይማኖት›› በጻድቁ ስም የተሰየመ ነው፡፡ በኬንያ የግብጽ ቤተክርስቲያን በስማቸው ገዳም አላት፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የግብጽ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትን መላክ ባቆመች ጊዜ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሾመው የነበሩ አባት ናቸው፡፡ በቤተ መንግሥቱ ወገንም ጸንቶ ለኖረው ‹‹እሥራኤላዊ›› መንግሥት እንደ የበላይ ጠባቂ፣ የመንግሥቱ መላሽና የሥርዓቱ አጽኚ ሲታዩ፣ በእርሳቸው መንበር የተተኩ እጨጌዎችም ፖለቲካውን ከነገሥታቱ ባልተናነሰ ሲዘውሩ የኖሩ ናቸው፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ አማካኝነት ወደ ሥልጣን የመጣው ሥርወ መንግሥት ለመንግሥቱ ጽናት ከክብረ ነገሥት ትርክት ቀጥሎ እንደ መሠረት ሲጠቀም የኖረው የአቡነ ተክለሃይማኖትን ‹‹የመላሽነት ሚና›› መሆኑን ታሪከ ነገሥታቱና ዜና መዋዕሎቹ ይነግሩናል፡፡ በዚህም የተነሣ በጥንታውያኑ መዛግብት (በቤተ ክህነቱም በቤተ መንግሥቱም) ታሪካቸው ለተለያዩ ዓላማዎች ሲጻፍና ሲተረክ እንደኖረው ሁሉ በዘመናዊ የኢትዮ ጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናትም በብዙ ሊቃውንት ዘንድ የተጠኑና የተነገ ረላቸው አባት ናቸው፡፡ እነ አንቶኒዮ ዲ. አባዲ፣ አልሜዳ፣ ዲልማን፣ ኢግናዝዮ ጉይዲ፣ ቦሪስ ቱራየቭ፣ ኮንቲ ሮሲኒ፣ኤንሪኮ ቼሩሊ፣ ሐንቲንግፎርድ፣ ካፕላን፣ አይ. ካምፕቤል፣ ማሬሎሬና ዴኒስኖስቲነሲን ከውጭ፤ እነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ታደሰ ታምራት፣ ተስፋየ ገብረ ማርያምና ጌታቸው ኃይሌ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን አበርክተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ልዩ የሆነ ቦታ የሚመነጭ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹መሥራች አባቶች (Founding Fathers)›› ከሚባሉት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበው አንዱ ናቸው፡፡ እርሳ ቸውን መሠረት በማድረግ በትግራይ፣ በኤርትራ፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በሐረርጌ፣ በወላይታና በሌሎችም ቦታዎች ቀደም ብለው የተመሠረቱ ገዳማትና ቤተ ክርስቲያንን ያገለገሉ አበው አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የአኩስም መንግሥት ተዳክሞ በነበረበት ዘመን ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም ፈተና ገጥሟቸው ነበር፡፡ የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ይህንን ፈተና ተቋቁሞ እንደገና መነሣሣት እንዲፈጠር አስችሎ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ቤተ ክህነቱን እንደገና ካነሡት አባቶች አንዱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ በተለይም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደብረ ሊባኖስን ማዕከል አድርገው ሰሜንና ደቡቡን እንደገና ያገናኙ አባት በመሆናቸው ሚናቸው ላቅ ያለ ነው፡፡ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚሰጠው ክብርና የሚደር ስባቸውም ትችት ከዚህ ከላቀው ሚናቸው የሚነሣ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለመተቸትና በዚያውም መንገድ ለማፍረስ የሚነሡ ሰዎች ዒላማ ከሚያደርጉባቸው አበው አንዱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ብዙ ቅርንጫፍ ያላቸው ዛፍ፣ ሕንፃውን የተሸከመ መሠረት፣ ብዙ ተክል የሚያጠጣ ምንጭ ናቸውና፡፡ እርሳቸውን መምታት ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ መምታት ነው፡፡ በየጊዜው የተነሡና ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመለከተ የሚያሄሱ ሰዎች ትችታቸውን አብዝተው የሚያሳርፉባቸውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ትችቱ ብዙ ጊዜ በአራት ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡ 1. አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዛግዌ ወደ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሽግግር ሲደረግ ነበራቸው በተባለው ሚና፤ 2. አቡነ ተክለ ሃይማኖት በነበሩበት ዘመን፣ 3. የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ማንነት በተመለከተ እና 4. በገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ በተገለጡት ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ እስካሁን በተገኙት መረጃዎች መሠረት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የመጀመሪያውን ትችት ያቀረበው ፖርቹጋላዊው ኢየሱሳዊ ኢማኑኤል ዲ. አልሜዳ ነው፡፡ አልሜዳ እኤአ በ1580 ተወለደ፡፡ ወደ ኢየሱሳውያን ማኅበር የገባው በልጅነቱ ነው፡፡ ሥልጠናውን ከወሰደ በኋላ እኤአ በ1602 ዓም በሚሲዮናዊነት ወደ ሕንድ ተላከ፡፡ እኤአ በ1624 ዓም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ መጀመሪያ ወደ ምጽዋ ከደረሰ በኋላ በመቀጠልም ወደ ፍሬሞና ገባ፡፡ እርሱ ኢትዮጵያ ከመድረሱ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ዐፄ ሱስንዮስ ካቶሊክነትን ተቀብሎ ስለነበር አልሜዳን በደስታ ነው የተቀበለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት በጣና ዙሪያ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትን በተለይም በትናንሽ የጣና ሐይቅ ደሴቶች ውስጥ በመትከል ይታወቃል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተዘዋወረባቸው ቦታዎችም አያሌ የብራና ጽሑፎችን ሰብስቦ ወስዷል፡፡ የሱስንዮስ ተተኪ የነበረው ንጉሥ ፋሲለደስ ኢየሱሳውያንን እኤአ በ1633 ከሀገር ባስወጣ ጊዜ ከኢማኑኤል ባራዳስ ጋር በመሆን ወደ ጎአ ሄዶ ፋሲለደስን ለመውጋት የፖርቱጋልን ርዳታ ሽቶ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካለትም፡፡ በመጨረሻም ወደ ሕንድ ተጉዞ በዚያው ከኖረ በኋላ በ1646 እኤአ በዚያው ዐረፈ፡፡ አልሜዳ ጎርጎራ እያለ በ1628 እኤአ ‹‹Historia de Etiopía a Alta ou Abassia›› የተሰኘ መጽሐፍ ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር፡፡ መጽሐፉ የተጠናቀቀው ከ1643 እስከ 1645 እኤአ ባለው ጊዜ ውስጥ ጎአ ውስጥ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎች እኤአ በ1954 ‹‹Some Records of Ethiopia, 1593-1646›› በሚል ርእስ በሐክልዩት ማኅበር በቤኪንግሐምና ሐንቲግፎርድ አማካኝነት ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ታትሟል፡፡ አልሜዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አምርሮ የሚጠላ፤ ‹‹ኋላ ቀርና በኑፋቄ የተሞላች ናት›› ብሎ የሚከስ ኢየሱሳዊ ነው፡፡ በጽሑፎቹም ላይ ይህንን ነው ሲያን ጸባርቅ የኖረው፡፡ ከዚህ ጠባዩ አንጻርም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ቢተች የሚጠበቅ እንጂ የሚገርም አይደለም፡፡ አልሜዳ በገድሉ ላይ የተነሡ አንዳንድ ነገሮችን መሠረት በማድረግ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ8ኛው መክዘ እንጂ በ13ኛው መክዘ አልነበሩም ሲል ይጀምራል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ እርሳቸውን ከ13ኛው መክዘ አያይዞ የሚተረኩ ትርክቶች ትክክክል አይደሉም ሲል ይገልጣል፡፡ ስለዚህም እኛ በገድላቸው የምናከ ብራቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያልነበሩ ሰው ናቸው ይላል አልሜዳ፡፡ እነ ፓድሮ ፓኤዝም ገደለ ተክለ ሃይማኖትን የተመለከቱ ትችቶችን በዘመኑ ሰንዝረው ነበር፡፡ የእርሱን ሂስ ከእርሱ በኋላ የተነሡትና ለካቶሊክ አስተምህሮ ያደላሉ የሚባሉት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም አጠንክረው ቀጥለውበታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከሀገር ቤት ሊቃውንት ወገን ጠንከር ያለ ትችት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የሰነዘሩ ሊቅ ናቸው፡፡ የእርሳቸው ትችት በዋናነት ያተኮረው፤ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖትና እጨጌው ተክለ ሃይማኖት ይለያያሉ፤ በሚለው ሐሳብ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ሐሳባቸው ቀደም ብሎ አልሜዳ ያነሣቸውን ሐሳቦች በመያዝ የራሳቸውንም አስተያየት ጨምረ ውበታል፡፡ ይህ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መከራከሪያ በኋላ ዘመን ‹‹ተሐድሶአውያን›› የሚባሉት ወገኖች ላነሷቸው ሐሳቦች መሠረት ሆነዋል፡፡ የአልሜዳንና የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ሐሳቦች መሠረት አድርገው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ ትችት የሚሠነዝሩት ሌሎቹ ቡድኖች ደግሞ ‹‹ተሐድሶአውያን›› ናቸው፡፡ ‹‹ተሐድሶአውያን›› የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ሐሳብ በመያዝ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን የተመለከቱ ሌሎች ትችቶችን ጨምረውበታል፡፡ ቀደም ብሎ በ17ኛው መክዘ የነበሩት ኢየሱሳውያን ያነሷቸውን ገድለ ተክለ ሃይማኖትን የተመለከቱ ትችቶችን በማጠናከር ሃይማኖታዊ መልክ አስይዘው አምጥተዋቸዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን ‹‹ተሐድሶአውያኑ›› በሁለት ታላላቅ ልሂቃን ላይ የከፋ ትችት ያወርዳሉ፡፡ በአቡነ ተክለ ሃይማኖትና በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ላይ፡፡ ሁለቱን ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር እምነታቸውና ለሀገር አንድነት የሠሩት ሥራ ነው፡፡ ትችቱም የሚወርድባቸው በዚህ የተነሣ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ትችት የሚሠነዝሩት ሌሎቹ ቡደኖች ደግሞ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ የፖለቲከኞች ትችት በዋናነት የሚያተኩረው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዛግዌና ሰሎሞናዊ መንግሥት ሽግግር ጊዜ ተጫውተውታል በሚባለው ሚና ላይ ነው፡፡ ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ወደ ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት በተደረገው ሽግግር ላይ፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነበራቸው የሚባለው ሚና፤ ንጉሣዊውን ሥርዓት ለማጽናት ሲባል በአንዳንድ የገድላት ቅጅዎችና ይበልጥ ደግሞ በታሪከ ነገሥትና ዜና መዋዕሎች ላይ በስፋት ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትለው እንደነ ጄምስ ብሩስ ያሉ ወደ ሀገሪቱ መጥተው የጻፉ ሰዎችም ተቀብለው አስተጋብተውታል፡፡ ይሄ ጉዳይ እስከ 20ኛው መክዘ ድረስ በነበሩ ጸሐፍት ዘንድ በበጎ የሚታይ ነበር፡፡ ከዜና መዋዕል ጸሐፊዎች እስከ ኅሩይ ወልደ ሥላሴና ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ድረስ በዚህ ሐሳብ ቀጥለው ነበር፡፡ ቅሬታ ይቀርብበት የነበረው ከአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ነበር፡፡ በተለይም በላስታ አካባቢ የሚገኙ የኋላ ሊቃውንት ጉዳዩን በቅሬታ ያነሡት ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ ጠንካራ ትችት መቅረብ የጀመረው ከ20ኛው መክዘ በኋላ በተለይም ከ1966 ዓ.ም. አብዮት በኋላ ነው፡፡ ከ1966 ዓ.ም. በኋላ የሚታተሙ መንግሥታዊ ድርሳናት አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመንግሥት መላሽነት ነበራቸው የሚሉትን ሚና በማንሣት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመተቸት ተጠቀሙበት፡፡ የሲሦ መንግሥት ጉዳይም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ፊውዳ ላዊነት እንደ ማሳያ ቀረበ፡፡ ይህ ትችት በ1983 ዓ.ም. መንግሥት ሲቀየርም አልተ ቀየረም፡፡ አሁን ያለው ሥርዓትም በየአጋጣሚው ይህን ጉዳይ ያቀነቅነዋል፡፡ በየድር ሳናቱም ያነሣዋል፡፡ ‹‹ጋላሕቲ ሰጊ›› የተሰኘውና የሕወሐትን ተጋድሎ የሚዘክረው መጽሐፍ፤ ‹‹በይኩኖ አምላክና በጻድቁ ተክለ ሃይማኖት (ከአማራ) የተጠነሰሰው የሰሎሞን ሥርወ መንግሥትን ዳግም የማምጣት ውጥን በአንድ በኩል የሁለቱን ሴማዊ ዝርያ ያላቸውን ሕዝቦች (ትግራዎትና አማራ) አዲስ ግንኙነት ሲያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃን በአቢስንያ መንግሥት ላይ ገናን ለመሆን የሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ የጀመሩበት ወቅት ነበር›› ይላል፡፡ የሚገርመው ነገር የገድላቱ ቅጅዎች የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን የዘር ሐረግ ከኢየሩሳሌም ትግራይ፣ ከትግራይ አምሐራ ሳይንት፣ ከአምሐራ ሳይንት ጽላልሽ/ ዞረሬ ድረስ እየተረኩት፣ ርግጠኛ ሆነው የዚህ ዘር ናቸው የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ለዚያን ዘመን አሠፋፈር የዛሬን ክልላዊ የጎሳዎች ቦታ መስጠት ስሕተት ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ዛሬ ጽላልሽ ኦሮምያ ክልል ውስጥ ናት፡፡ ይህ አቡነ ተከለ ሃይማኖትን በተመለከተ የተዘጋጀው መጽሐፍ ዓላማ እነዚህ ትችቶች ያነሷቸውን የተሳሳቱ ሐሳቦች በታሪካዊና በሃይማኖታዊ ሰነዶች መነሻነት ለመሞገት ነው፡፡ እግረ መንገዱንም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ልዩ ልዩ መረጃዎች የተካተቱበት አንድ ድርሳን ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ልዩ ልዩ የገድላት ቅጅዎች፣ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መረጃ የሚሰጡን ሌሎች ገድላት፣ ስንክሳሮችና ድርሳናትን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ዜና መዋዕሎች፣ ታሪከ ነገሥቶች፣ የተጓዦች የታሪክ ሰነዶች ታይተዋል፡፡ የጸሎት መጻሕፍት፣የዜማ መጻሕፍትና በየዘመናቱ የተሣሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕሎች ተዳሰዋል፡፡ በዘመናውያን የታሪክና የፊሎሎጂ ሊቃውንት የተጠኑ የጥናት ድርሳናት ተመሳክረዋል፡፡ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የተያያዘ ታሪክ ባላቸው ቦታዎች ላይ የመስክ ሥራ ተሠርቷል፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ አንድ ወጥ የጥናት ድርሳን ለማቅረብ የተሞከረው በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣ የምክሐ ደናግል ማርያም መንፈሳዊ የወጣቶች ማኅበር በኩል በ2008 ዓ.ም. የተዘጋጀው ‹‹አውሎግሶን፣ ሕይወቱ ወገድሉ ለብጹዓዊ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት›› የተሰኘው ነው፡፡ መጽሐፉ በአብዛኛው ተችዎች ለሚያነሡት ሃይማኖታዊ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡ የገድላቱን ቅጅዎች፣ ታሪካዊ ሰነዶችና ሌሎች መረጃዎችን ለመዳሰስ አልሞከረም፡፡ የመጽሐፉ መዘጋጀት አንዱ ዓላማም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ሲዘጋጅ እንደ መነሻ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚነ ሡትን ሐሳቦች የሚዳስስ ምዕራፍ ተካትቷል፡፡ በመቀጠልም አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና ሥራቸውን በሚገባ ለማየት እንዲቻል ከእርሳቸው በፊትና በእርሳቸው ዘመን የነበረቺውን ኢትዮጵያ፣ በእርሷም ውስጥ የነበረውን የእምነት ተዋስኦ የሚያሳይ ክፍል አለ፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ከታሪክ፣ ከፊሎሎጂ፣ ከሥነ ጽሑፍና ከሃይማኖት አንጻር ለማየት እንዲቻል ገድላትን በተመለከተ የሚያብራራ ምዕራፍም ተካትቷል፡፡ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መረጃ የሚሰጡንን የመጀመሪያ ደረጃ መዛግብት የተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያም አለ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ልዩ ልዩ የገድላቱ ቅጅዎች፣ የስን ክሳር ቅጅዎች፣ ዜና መዋዕሎችና ታሪከ ነገሥቶች፣የጸሎትና የዜማ መጻሕፍት፣ የተጓዦች ድርሳናትና ሌሎችንም የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ይገኛሉ፡፡እነዚህ ሁሉ በቀዳሚነት ከቀረቡ በኋላ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን የሕይወት ታሪክ በማስ ረጃ በተደገፈ መንገድ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ማንነት ለማጥናት የተሞከረው በሁለት መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው መንገድ ቀዳሚው ሥራ እርሳቸውን በተመለከተ የሚተረከውን የተለመደውን አተራረክ በመከተል (በተለይም የደብረ ሊባኖሱን ቅጅ አተራረክ) ዐጽመ ታሪኩን መመሥረት ነው፡፡ ነገር ግን እርሳቸውን የተመለከቱ መረጃዎች በተለያዩ መዛግብት ተበትነው በመገኘታቸው የገድላቱ ቅጅዎችም የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም በተለያዩ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎችን በዐጽመ ታሪኩ ውስጥ ምክን ያታዊ በሆነ መንገድ በማስገባት አንድ ወጥ ፍሰት አንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መልኩም በየመዛግብቱ የተበታተነው ጻድቁ አቡነ ተክለ ተክለ ሃይማኖትን የተመለከተው መረጃ በአንድ ወጥ ዐጽመ ታሪክ ውስጥ ሥግው ሆኗል፡፡ የመጀመሪያው መንገድ ሁለተኛው ሥራ ደግሞ የገድላቱ ቅጅዎች፣ ሌሎች መዛግብትና ድርሳናት በአንድ ጉዳይ ላይ በሚለያዩበት ወቅት ብያኔ መስጠት ነው፡፡ ብያኔ ማለት በተጠየቅ፣ በእምነት ሥርዓት፣ በተለምዶ አሠራርና በታሪካዊ ሰነዶች መነሻነት፤ የትኛው አገላለጥ፣ አተራረክ ወይም ኩነት የተሻለ ተቀባይነት አለው? የሚለውን መተቸት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የኋለኞቹን የገድሉን ቅጅዎች ከቀደምቱ ማነጻጸር፣ ገድላተ ተክለ ሃይማኖትን ከሌሎች ገድላት ጋር ማነጻጸር፣በገድላቱ ላይ የተጠቀሱ ታሪኮችን፣ ሐሳቦችንና ኩነቶችን ከሌሎች ታሪካዊ ሰነዶችና የታሪክ ጥናቶች ጋር ማነጻጸር፣መረጃዎቹን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነባር ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም አስተምህሮ ጋር ማነጻጸር፣ ብሎም ከተለምዶ አሠራሮች፣ ከይትበሃሎችና ከሀገር ባህል ጋር ማነጻጸር አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንድን ገድል በመነሻነት አልተጠቀምኩም፡፡ የደብረ ሊባኖሱን ቅጅ ዐጽመ ታሪክ ከመውሰድ በቀር፡፡ የደብረ ሊባኖሱን ቅጅ ዐጽመ ታሪክ የወሰ ድኩበት ምክንያት ከሌሎቹ ቅጅዎች በተለየ ሰፊና አካታች በመሆኑና በብዛትም የተሠራጨ በመሆኑ ነው፡፡ የታሪኩ ስፋት ከአዛርያስ እስከ ተክለ ሃይማኖት፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ደብረ ሊባኖስ፣ ከሰሎሞን እስከ ይኩኖ አምላክ ይደርሳል፡፡ ስለዚህም ታሪኩን ለማጥናት የተሻለ ነው፡፡ ያ ማለት ግን በያዛቸው ታሪኮች ከሌሎች የተሻለ ነው ማለት አይደለም፡፡ እርሱን በቦታው እናየዋለን፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ታሪክ በምንዳስስበት ጊዜ ለማድረግ የተሞከረው በእያንዳንዱ የታሪክ ኩነት ላይ ልዩ ልዩ ቅጅዎች የሚገልጡትን መመልከት፣ እነርሱንም በሌሎች መዛግብት ማሟላት ወይም ማመሳከር፣ በመጨረሻም በተለያዩት ቅጅዎች አተራረክና ሐሳብ ላይ ብያኔ መስጠት ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክና እርሳቸውንም ከተመለከቱ አጋር ታሪኮች ጋር በተያያዘ ለሚነሡ ሐሳቦች፣ ኩነቶች፣ የታሪክ ተዋንያን፣ ቦታዎች፣ አባባሎች፣ ሥርዓቶች፣ የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነቶች፣ወዘተ ተጨማሪ መረጃዎችን መስጠት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው ከዘመናችን በራቀ ጊዜ በመሆኑ የቦታ ስሞች ተቀያይረዋል፤አንዳንድ ሥርዓቶችና ባህሎች ቀርተዋል፣ ተቀይረዋል፤ ሕዝቦች ቦታ ተቀያይረዋል፤ አስተሳሰቦች ተለውጠዋል ወይም ቀርተ ዋል፤ ገዳማትና አድባራት ፈርሰዋል፤ አንዳንድ ታሪካዊ ሰዎችም ወይ ተዘንግ ተዋል ወይም በአንድ አካባቢ ብቻ የሚታወሱ ሆነዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች የዛሬ አንባቢ ለመረዳት እንዲቻለው ተጨማሪ መረጃዎችን ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ የመጨረሻው የመጽሐፉ ክፍል አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ከገድላቱ የተለዩ ድርሳናት በአባሪነት የቀረቡበት ነው፡፡የዚህ ክፍል ዋና ዓላማው እነዚህ ታሪካዊ ድርሳናት በአንድም በሌላም መልኩ ከቅዱሱ ታሪክ ጋር የተገናኙ ናቸውና እነርሱን በምልዐት በማቅረብ የተሟላ ሥዕል እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ እርሳቸውን የተመለከቱ ዋና ዋና ድርሳናትን በአንድ መዝገብ ማሰባሰብም ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ግን እነርሱ የያዙትን ነገር በተጨማሪ ታሪኮች በማብራራት ነው፡፡ አንዳንዶቹንም በማሆን (አሁን ባሉን መረጃዎች መሠረት እንደገና በመሥራት) ነው፡፡ ለምሳሌ የኤንሪኮ ቼሩሊን የደብረ ሊባኖስ አበምኔቶች ዝርዝር ጥናት በአዳዲስ መረጃዎች ለማሆን ተሞክሯል፡፡ በአጠቃላይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማናቸው? እርሳቸውን በተመለከተ ከልዩ ልዩ ወገኖች ሲቀርቡ የኖሩትና የሚቀርቡት ትችቶች ተገቢ ናቸውን? ትችቶቹ እንዴት ሊነሡ ቻሉ? መዛግብቱስ ትችቶቹን በተመለከተ ምን ይነግሩናል? የሚሉትን በተመለከተ ይህ መጽሐፍ በዕውቀታችን ላይ አንዳች ነገር ይጨምራል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ሊቁ አባ ባሕርይ ዘሀገረ ጋሞ በመዝሙረ ክርስቶስ ድርሳኑ መግቢያ ላይ ‹የሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ በሁለተኛዋ መልእክቱ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምስክር ጠቀሰ፤ ጳውሎስም ከመጻሕፍት ሁሉ መልእክታቱን አቀናበረ፤ እርሱ ራሱ ልሳነ ክርስቶስ ተብሎ ሳለ ከሌሎች ቅዱሳን ትምህርቶች ምስክር ጠቀሰ፡፡ እኔም ስለዚሁ ምክንያት ይህንን መጽሐፈ ድርሳን ከብዙ መጻሕፍት ምስክር አምጥቼ አዘጋጀሁ፡፡ በደካማው ልቡናዬ በዐቅሙ መጠን› እንዳለው ይህንንም መጽሐፍ አሉ ከተባሉት ማስረጃዎች አንጻር ለማየት ተሞክሯል፡፡

No comments:

Featured Posts

“ግብፅ ግድቡን የሚመታ ራፋል የተባለ የጦር አውሮፕላን ገዝታ ነበር” የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም የተወለዱት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ የጁ ወረዳ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው። የልጅነት ጊዚያቸው...

Blogger